የቢሮው አመሰራረት

የደቡብ ብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት የክልላችንን የኢኮኖሚ ዕድገት በላቀ ደረጃ ለማፋጠን የአስፈፃሚ አካላት አደረጃጀት የተልዕኳቸውን ስፋትና ተቀራራብነት መሰረት ያደረገ እንዲሆን በማስቻል የቀረጻቸዉን ስትራቴጂዎች እንዲያስፈጽሙ በክልሉ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን በወጣው አዋጅ ቁጥር 161/2008 መሰረት ከተቋቋሙት መስሪያ ቤቶች መካከል የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
 
በዚሁ መሰረት ቢሮው በአዲሱ አዋጅ የተሰውን ስልጣንና ተግባር በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ በማድረግ በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፍ እመርታ በማስመዝገብ በኢኮኖሚ አወቃቀር ላይ ጉልህ ትራንስፎርሜሽን እንዲመጣ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ዘርፉ በክልሉ ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ የሚኖረውን ሚና የበለጠ ለማሳደግ እና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልማት እንዲኖር ብሎም የንግድና ግብይት ሥርዓቱን በማሳለጥ ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የአርሶ/አርብቶ አደሩንና የግብይት ተሳታፊውን ኑሮ የሚያሻሽልና የዜጎችን እኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻልና መሰል ተግባራቶችን ተቋማዊ በሆነ አግባብ እንዲፈጸሙና ይህንንም የሚያስፈጽሙ አካላቶችን በመመደብ ለማሰራት፣ ሥራዎችን ተገቢነት ያለውን ፍሰት ተከትለዉ እንዲደራጁ ለማድረግ አደረጃጀቱን መከለስና በአዲስ መልክ ማደራጀት አስፈልጓል፡፡
 
ስለሆነም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ቀድሞ የነበረዉ የን/ኢ/ከ/ል/ቢሮ እና የግብይትና ህ/ሥራ ቢሮ አደረጃጀቶች በተሟላ ሁኔታ ተደረሽ ማድረግ ያልቻሏቸውን ስትራቴጂያዊ ጉዳዮችና የትኩረት መስኮች በመዳሰስና ያለዉን አሰራር በመፈተሽ በተግባር ውስጥ የታዩ ችግሮችን ሊፈታ የሚችል እንዲሁም በክልሉ የጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ልማት ለኢንዱስትሪ ዘርፍ ልማት ዋናው የትኩረት አቅጣጫ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያስችል እና የነጻ ገበያ መርህን የተከተለ የንግድና ግብይት ሥርዓትን በማስፋፋት ለአምራቹ፣ ለሸማቹና ለንግዱ ማህበረሰብ የተቀላጠፈ ግልጽና ፍትሃዊ አገልግሎት በመስጠትና ተጠቃሚነታቸውን በማረጋገጥ የተሻለ የውጭ ምንዛሪ እንዲኖርና ዜጎች አስተማማኝ የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለማድረግ የተጣለውን ግብ የማሳካት ታላቅ ኃላፊነት መወጣት የሚያስችሉ አደረጃጀቶችን በመለየት፣ የፌደራል መስሪያ ቤቶችንና የሌሎች ክልሎች ተመሳሳይ አደረጃጀቶች ልምዶችን በመቀመር የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ሴክተር አደረጃጀት ከክልል እስከ ታችኛው እርከን ድረስ የሚኖረውን ዋና ዋና መዋቅራዊ አደረጃጀት እንዲያሳይ ተደርጎ የተዘጋጀ ሲሆን ረቂቅ የጥናት ሰነዱ በቢሮው ማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ተገምግሞና አስተያየት ተሰጥቶበት ለርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ውሳኔ በሚከተለው አግባብ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ የተደረገ ነው፡፡