የክልሉ ን/ገ/ል/ቢሮ ም/ኃላፊ እና የንግድ አሰራርና ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ

የሀገራችንን ልማትና ዕድገት ቀጣይነት በማረጋገጥ የበለፀገች ኢትዮጲያን ለመገንባት በምናደርገው የለውጥ ጉዞ የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ሴክተር ፍትኃዊ  ቀልጣፋና የዘመነ የንግድ አሰራር ስርዓት ለማስፈንና ህገ-ወጥ ንግድን ለመቅረፍ የድርሻውን በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት ሀገራችን ወደ ብልፅግና ለምታደርገው ጉዞ መሰረት ለመጣል ዘርፈ-ብዙ የለውጥ እንቅስቃሴ እተደረገ ይገኛል፡፡ይህንን ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ እና የሀገር ግንባታ ሂደት አጠናክሮ ለማስቀጠል የዜጎች ተሳትፎ ማጎልበት፣ የመንግስትና የግሉ ሴክተር አጋርነትን ማጠናከር፤አስተማማኝ ሰላም ማረጋገጥና ልማትን ማፋጠን ወሳኝ ይሆናል፡፡

ባለፉት አመታት የንግዱ ስርዓት የዘመነ ጠንካራና ውጤታማ እንዲሆን ለማድረግና የንግድ ስርዓታችንን ለማዘመን በየነ-መረብ የንግድ አሰራር ስርዓት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር በርካታ የሪፎርም ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም እየሰፉ የመጡ መሻሻሎች ታይተዋል፡፡ አመርቂ ውጤቶችም ተገኝተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁንም ፍትኃዊ ቀልጣፋ እና አገልግሎት የዘመነ  የንግድ ሥርዓት ለማስፈን ህገ-ወጥ ንግድና የኮንትሮባንንድ እንቅስቃሴን ለመግታት ትኩረት የሚሹ ተግዳሮቶች በርካታ ናቸው፡፡ በንግድ ስርዓቱና በገበያው ውስጥ ሰፊ ድርሻ እና ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እያላቸው ወደ ታክስ ስርዓቱ ያልገቡ፣ ህጋዊ ፈቃድ አውጥተውና ቋሚ አድራሻ ይዘው የማይሰሩና በህጋዊ ነጋዴው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ኃላፊነት በጎደለው ሁኔታ በአቋራጭ ለመክበር የሚተጉና የንግድ ውድድር ሚዛኑን የሚያዛቡ በርካታ አካላት አሉ፡፡ህገ-ወጥ ንግዱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱና የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴም ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በተለይም በኮንትሮባንድ የሚገቡ ደረጃቸውን ያልጠበቁ፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ለህብረተሰቡ ለጤናና ደህንነት አስጊ የሆኑ ምግብና፣ መድሀኒት ፣ አደንዛዥ ዕፅ፣ አልባሳትና የጦር መሳሪያ ጭምር ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ህጋዊውን የንግድ ሥርዓት በማወክ ህጋዊ ነጋዴዎች ከስርዓቱ እንዲወጡ በማድረግ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል እንዳይኖር ከማድረጉም ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌለው የዋጋ ንረትና የንግድ አሻጥር ዜጎችን እያማረረ ይገኛል፡፡ የፀጥታና የደህንነት ስጋት የሆኑ ሸቀጦች ድንበር አልፈው ይገባሉ፡፡

እነዚህ በንግድ ስርዓቱ ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ህገ-ወጥ ድርጊቶች የሀገሪቱ ብሎም የክልሉን ኢኮኖሚ እንዲዳከም የሚያደርጉና የንግድ ውድድርና ስርዓቱን የሚያቀጭጩ ከመሆኑም በላይ በዚህ ድርጊት የተሰማሩ አካላት ድርጊታቸው ህገ-ወጥ እንደመሆኑ መጠን ሀገራዊም ሆነ ክልላዊ ሰላምና መረጋጋት እንዳይፈጠር ከማድርግ አንፃር የጥፋት ድርጊታቸው ከፋ እያደረገው  ነው ፡፡

ስለሆነም ይህ ሁኔታ በጋራ ርብርብና በጠንካራ ቅንጅት መቀልበስ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ለማረም ባገባደድነው ዓመትም ሆነ ባለፉት ዓመታት መንግስት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት በአስፈፃሚ ተቋማቱ የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም  በሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ጠንካራ ቅንጅት ሲፈፀም የነበረ ባለመሆኑ አመርቂ ውጤት ሊያስገኝ አልቻለም፡፡ በመሆኑም  ሕገ-ወጥነት  ለማንም  የማይጠቅምና ጉዳቱ  የከፋ  ስለሆነ የፍትህ፣ የገቢዎች ፣ የጸጥታ  አካላትና ሌሎችም  ባለድርሻ አካላት  በጋራና በተቀናጀ ሁኔታ  ልንገታው  ይገባል፡፡ዋጋ ንረትን የሚያራግብ የግብርና ምርታማነት በማሳደግ ሕገ-ወጥ የምርት ዝውውር በተቀናጀ ቀጣይነት ባለው መልኩ አካላት ርብርብ ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም አሁን ላይ የንግድ አሰራር ስርዓቱ የዘመነ ቀልጣፋና ለአሰራር ምቹ ከኪራይ ሰብሳቢነት የፀዳ የአሰራር ስርዓት የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ ፣እድሳትና የክፍያ ስርአት በe-trade በሞባይል  ስልካቸው ቤታቸው  ሆነው አገልግሎቱን ማግኘት  የሚችሉበት የኦንላይን  ስራ  በተቀላጠፈ መልኩ ወደ ስራ ተገብቶ በመተግበር ላይ መሆኑንና እንዲሁም የገበያ መረጃ የነፃ ስልክ 6077 እና በቀጣይም አዲስ የገበያ መረጃ ሶፍተዌር እየተዘጋጀ እንደሆነ እያሳስብኩ ተጠቃሚ መልካም እድል መፈጠሩን እገልፃለሁ፡፡

     አመሰግናለሁ!!